| ← 1Chronicles (10/29) → |
| 1. | ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ተዋጉ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ተወግተውም በጊልቦአ ተራራ ላይ ወደቁ። |
| 2. | ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን በእግር በእግራቸው ተከትለው አባረሩአቸው፤ ፍልስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ። |
| 3. | ሰልፍም በሳኦል ላይ ጠነከረ፥ ቀስተኞችም አገኙት፤ ከቀስተኞችም የተነሣ ተጨነቀ። |
| 4. | ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን። እነዚህ ቈላፋን መጥተው እንዳይዘብቱብኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ነበርና እንቢ አለ። ሳኦልም ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ። |
| 5. | ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል እንደ ሞተ ባየ ጊዜ እርሱ ደግሞ በሰይፉ ላይ ወድቆ ሞተ። |
| 6. | ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ የቤቱም ሰዎች ሁሉ በአንድ ላይ ሞቱ። |
| 7. | በሸለቆውም የነበሩት የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንደ ሸሹ፥ ሳኦልና ልጆቹም እንደ ሞቱ ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው። |
| 8. | በነጋውም ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ በመጡ ጊዜ ሳኦልንና ልጆቹን በጊልቦአ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው። |
| 9. | ገፈፉትም፥ ራሱንና መሣሪያውንም አንሥተው ለጣኦቶቻቸውና ለሕዝቡ የምሥራች ይወስዱ ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ዙሪያ ሰደዱ። |
| 10. | መሣሪያውንም በአምላኮቻቸው ቤት ውስጥ አኖሩ፤ ራሱንም በዳጎን ቤት ውስጥ ቸነከሩት። |
| 11. | የኢያቢስ ገለዓድም ሰዎች ሁሉ ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን ሁሉ በሰሙ ጊዜ፥ |
| 12. | ጽኑአን ሰዎች ሁሉ ተነሥተው የሳኦልን ሬሳ የልጆቹንም ሬሳ ወሰዱ፥ ወደ ኢያቢስም አመጡአቸው፤ በኢያቢስም ካለው ከትልቁ ዛፍ በታች አጥንቶቻቸውን ቀበሩ፥ ሰባት ቀንም ጾሙ። |
| 13. | እንዲሁ ሳኦል በእግዚአብሔር ላይ ስላደረገው ኃጢአት፥ የእግዚአብሔርንም ቃል ስላልጠበቀ ሞተ። ደግሞም መናፍስት ጠሪ |
| 14. | ስለ ጠየቀ እግዚአብሔርንም ስላልጠየቀ፥ ስለዚህ ገደለው፥ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት አሳለፈው። |
| ← 1Chronicles (10/29) → |